1. ፕሬዚዳንቱና የክልሉ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባራቸውን ማከናወን እንዲችሉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ 2. ከመሥሪያ ቤቶች የሚመነጩ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን ያስተባብራል፤ ይተነትናል፤ ለክልሉ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል፤ 3. የክልሉ መንግሥት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና የልማት ፕሮግራሞች አፈጻጸምን ይከታተላል፤ ይደግፋል፤ 4. ለፕሬዚዳንቱ ወይም ለክልሉ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት የሚቀርቡ የተለያዩ የውሳኔ ሐሳቦችን ያጠናል፤ ይተነትናል፤ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል፤ ሲወሰኑም ይፈጽማል፤ ያስፈጽማል፤ አፈጻጸማቸውን ይከታተላል፤ አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል፤ 5. የአስተዳደር ጉዳዮች፣ የሕዝብ አቤቱታና ቅሬታ የሚስተናገዱበትን ሥርዓት ይዘረጋል፤ አፈጻጸሙን ይከታተላል፤ በተለያዩ ዘዴዎች ሕዝቡ እንዲያውቀው ያደርጋል፤ ዝርዝር አፈጻጸሙ በሚወጣ ደንብ ይወሰናል፤ 6. ከባለጉዳዮች የሚቀርቡ አቤቱታዎችንና ጥያቄዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል፤ ምላሽ ይሰጣል፤ በእርሱ ደረጃ መፍትሔ ማግኘት የማይችሉትን ለፕሬዚዳንቱ ወይም ለክልሉ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት ወይም ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ውሳኔ እንዲያገኙ ያደርጋል፤ 7. የሕዝብ ቅሬታዎችን ዓይነት፣ ብዛትና መንስኤ በየጊዜው በማጥናት ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር ለውሳኔ ሰጪው አካል ያቀርባል፤ 8. ለፕሬዚዳንቱና ለክልሉ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤት የፕሮቶኮልና የዶክመንቴሽን አገልግሎት ይሰጣል፤ 9. የዳያስፖራ ጉዳዮች ተሳትፎ፣ ክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን ያከናውናል፤ 10. በክልሉ መንግሥት አስተዳደር ምክር ቤትና በፕሬዚዳንቱ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል።