የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ክልሉን ይመራል፣ ሕዝቡንም ይወክላል።
ፕሬዚዳንት
የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ክልሉን ይመራል፣ ሕዝቡንም ይወክላል።
ፕሬዚዳንት
ክቡር ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ
ስለ እኛ
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት መልእክት
ኦሮሞ በሺዎች በሚቆጠሩ ዓመታት በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ያልተቋረጠ ትግል አልፎ ድሎችን በማስመዝገብ፣ ለሀገርና ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ማንነት — የገዳ ሥርዓት ፖለቲካና አስተዳደር፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አካታችነትና መቻቻል — ይዞ እዚህ ደርሷል። ዛሬም ኦሮሞ ምሳሌ በሆነው ሥርዓቱ፣ እሴቱና ባህሉ በዚህ የትግል ምዕራፍ የገጠሙትን ችግሮች እንዴት እንደሚሻገር ከታሪኩና ከሥርዓቱ ጠንቅቆ ያውቃል። የምንገኝበት የትግል ምዕራፍ በማንኛውም መመዘኛ ልዩ ነው። ባለፉት ሥርዓቶች ኦሮሞ ለሀገር ድል ያስመዘገበበት ማንነቱ እንደ ወንጀል ሲቆጠር፣ ሀገርን ያቆመው የድል ታሪኩም ሲፋቅ እንደነበረ በግልጽ በመረዳትና በመተንተን፣ መልሶ በመጨበጥ የያዝነውን ሀገር ለማሻገር በትጋት እየሠራን ባለንበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። በሌላ በኩል በደረስንበት የትግል ደረጃ የሕዝባችንን የትናንት ታሪክ በደልና ስሜት ለቡድንና ለግል ፍላጎት እንዲመች ለመጠቀም የሚደረገውን ሙከራ በማክሸፍ፣ በአግባቡ የተደገፈና የጸና የሕዝብና የሀገር ድል ለመገንባት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። እነዚህ አካላት ያለንበትን ሁኔታ በማጋነንና በማጣመም ፍላጎታቸውን ማሳካት ሲያቅታቸው፣ በሌላ በኩል ጠንካራ የኦሮሞ ውስጣዊ አንድነት እንዳንገነባ፣ ለዚህ ታላቅ ሕዝብ የሚመጥን የትግል ደረጃ ላይ እንዳንደርስና የያዝነውን ሀገር እንዳናሻግር ሕዝብንና መንግሥትን እረፍት በመንሳት ባረጀ ፍላጎት ይታገላሉ። ከሁሉም በላይ እንደ ሀገር ልንሸከመው በሚገባን የውጭ ጫና ውስጥ ለኦሮሞና ለኦሮሚያ በማይመጥን ዓላማ ሕዝባችንን ለማደናገር፣ የሀገር ግንባታ ኃይል እንዳይሆን፣ ከዚህም አልፎ በውድ መስዋዕትነት በገነባው መንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚሠራው ሥራ ሰፊ ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሕዝብና በሀገር ዓላማ ላይ የተቃጣውን የግፍና የሴራ ኃይል በማክሸፍ፣ ያለንበትን ሁኔታ ከማንም በላይ የሚረዳውን ሕዝባችንን ይዘን ከፍተኛ ደረጃ ድል በማስመዝገብ የማይካድ ታሪክ መገንባታችንን እንቀጥላለን። ይህ ዓመት ብዙ ለውጦችን የምናስመዘግብበትና የምናሳካበት ዓመት ነው። በአንድ በኩል ሕዝባችን በልጆቹ መስዋዕትነት የቆመውን፣ የወደፊት ዕጣ ፈንታውን የሚያስተዳድረውን የመንግሥት ሥርዓት የሚመርጥበትና የሀገርን ታሪክና ሥርዓት በመገንባት ረገድ ድርሻውን የሚወስንበት ነው። በሌላ በኩል ለቀጣዩ ምዕራፍ «ድህነትን ታሪክ ለማድረግ» በምንሠራው ሥራ ውስጥ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት የምናከናውንበት ነው። ይህንን ለማድረግ የሚገጥሙንን ውስጣዊና ውጫዊ ትግሎች በድል እንድንሻገር የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሙሉ እምነት ይሠራል። በአጠቃላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የትኩረት ሥራዎች ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት፣ ኦሮሚያ የምትናፍቀውን ሰላም መፍጠር፣ ኦሮሞና ኦሮሚያ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ድርሻ በግፍ ቡድኖች እንዳይነጠቅ መጠበቅ እና ብዝኃ ብሔራዊ፣ ሁሉን አካታች፣ የእኩልነትና የወንድማማችነት ፌዴራላዊ ሥርዓትን ማሳካት መሆናቸውን፣ ሕዝባችን የሰጠንን አደራ ለመወጣትና የጀመርናቸውን ድሎች ከግብ ለማድረስ ጠንክረን እንደምንሠራ በድጋሚ አረጋግጣለሁ። ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት